መልዕክት መልዕክት

Back

የዋና ሥራ አስፈጻሚ መልዕክት

በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ከግብ ለማድረስ የመላው ማሕበረሰብ፣ የእያንዳንዱ ዜጋ ብሎም የልዩ ልዩ ተቋማት ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ የህዝብ ሰላም እንዲጠበቅ እና የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁላችንም የለውጡ አካል ሆነን ይህን ታሪካዊ ተልዕኮ ለማገዝ የድርሻችንን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እንደ አንድ የልማት ተቋም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሀገራችን በሂደት ላይ የሚገኘውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ በኩል የተጣለበት ኃላፊነት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቤት አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ በሀገራችን እጅግ አንገብጋቢ እና አፋጣኝ ምላሽ ከሚሹ የልማት ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ችግር ሆኖ በመዝለቁ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኮርፖሬሽኑ ለመኖሪያ ቤት፣ ለንግድ፣ ለድርጅትና ለሌሎች ግልጋሎቶች የሚውሉ ቤቶችን በማቅረብ የተሰጠውን ድርሻ ለመወጣት እንዲችል የሚቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚል አዲስ ስያሜ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ በደንብ ቁጥር 398/2009 የተለያዩ ዓላማዎች ተሰጥተውት የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ እንደ አዲስ ሲቋቋም በተለይም በመዲናችንና በድሬዳዋ ከተማ የሚታየውን ከፍተኛ የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር በርካታ እና ፈርጀ ብዙ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡ በተለያዩ ስያሜዎች ሲጠራና የተለያዩ የሪፎርም ጎዳናዎችን ያለፈው ይህ አንጋፋ ተቋም ከተመሠረተ ከአራት አስርተ አመታት በላይ ያስቆጥር እንጂ የእድሜውንና ያለፈበትን ሪፎርም በሚመጥን ደረጃ ያላደገ፣ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይዞ ሲጓዝ የነበረ እና እጅግ በርካታ ውዝፍና መፍትሄ ሳይሰጣቸው ለዓመታት የቆዩ ችግሮች የነበሩበት ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ለነባር ችግሮች መፍትሄ የመስጠት፣ አንዳንድ የአሰራር ክፍተቶችን የመድፈን ሥራዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተጠናቀቀው በ2011 በጀት ዓመትም ትኩረት ተሰጥቷቸውና ተጠናክረው የቀጠሉ ሥራዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በ2011 በጀት ዓመት የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ በማጠናከርና ለውጥ ሠራዊት ግንባታችን ላይ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ከዚህ የላቁ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ስንሰራ ቆይተናል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመ በኋላ በተለይም ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ ተቋሙን እንደ አዲስ የማደራጀት፣ የሰው ኃይል የማሟላት፣ የሕግ ማዕቀፎችን የመቅረፅ፣ የቤት ልማት ሥራን ለመጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን የማከናወን ሥራዎች በዋናነት ከተከናወኑ እንቅስቃሴዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ ይዞታ ስር የሚገኙ ንብረቶችን የመለየትና በቀጣይም ለቤት ልማቱ የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት የሚያስችለውን የቤቶች ዋጋ ትመና (ቫሉዬሽን) እና የቤቶች ቆጠራን በማካሄድ የኮርፖሬሽኑን ቤቶች መረጃ በዘመናዊ ሁኔታ የማደራጀት፣ ለውሳኔ አሰጣጥ ዝግጁ የማድረግ እንዲሁም የንግድ/የድርጅት ቤቶች የኪራይ ተመን ማስተካከያ ማድረግ ከዋና ዋና ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2011 በጀት ዓመት በተለየ ሁኔታ ትኩረት ከሰጣቸው ሥራዎች መካከል አንደኛው የቤቶች ግንባታ ሲሆን ከ28 ዓመታት በላይ ከቤት ልማት ርቆ የነበረውን ተቋም ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚያስችሉት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የቤት ልማት ዘርፉን የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት፣ የሰው ኃይሉን የማሟላትና ለግንባታ ዝግጁ የማድረግ እንዲሁም የዲዛይን፣ የስታንዳርድ፣ የግንባታ አዋጭነት ጥናት የማከናወን እንቅስቃሴ ከመደረጉም ባሻገር ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የግንባታ ጨረታ በማውጣት ከአሸናፊ የግንባታ ተቋማት ጋር የውል ስምምነት ተፈጽሞ ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡

በመሆኑም በቤት ልማት ሂደት አጋጥመው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ለ2011 በጀት ዓመት ከተያዙ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች መካከል ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ ጨረታ በማውጣትና በ5 ሳይቶች ላይ አሸናፊዎችን በመለየት ባሸነፉት ኮንትራክተሮች አማካኝነት ግንባታውን ለማስጀመር የመጀመሪያው ዙር የግንባታ ማስጀመሪያ የውል ስምምነት ተከናውኖ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኮንሰልታንት ለማስገንባት የሚያስችል ጥናት በማድረግና በመንግስት የግዥ ስርአት መሠረት ምዘና በማከናወን የአማካሪ ምርጫ በማድረግ ተጨባጭ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

በሂደት ላይ የሚገኘው የቤት ልማት ሥራ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ህንጻዎችን በመገንባት በከተማችን የሚታየውን ከፍተኛ የቤት እጥረት ለመቅረፍ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ለሆነችው መዲናችን ገፅታ መሻሻል የሚጫወተው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት በየጊዜው እየገጠሙን ለሚገኙ ልዩ ልዩ መሰናክሎችና ውስብስብ ፈተናዎች ሳንበገር ከዚህ የላቀ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራውና ቀሪ ፕሮጀክቶችንም በቀጣይ ወራት ወደ ተግባር ለማስገባት የተቻለውን ሁሉ ጥረት የምናደርግ ይሆናል፡፡

ከቤት ግንባታ በተጨማሪ ባለፈው አንድ አመት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶትና የቅርብ ክትትል በማድረግ ሲከናወን የቆየው የንግድ/የድርጅት ቤቶች የኪራይ ትመና አንዱ ነው፡፡ በኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 398/2009 አንቀጽ 5 ንዑስ ቁጥር 8 እንተገለጸው “ለሚያስተዳድራቸው ቤቶችና ይዞታዎች የኪራይ ተመን ጥናት ማካሄድና ተግባራዊ ማድረግ” ነው፡፡

የንግድ/ድርጅት ቤቶች የኪራይ ትመናው ዋና ዋና ዓላማዎች፣ ሕጋዊነትን ማረጋገጥ፣ ጤናማ የገበያ ውድድርን ማጎልበት፣ ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ፣ የኪራይ ተመን አሰራሩን ማስተካከልና ዘመናዊና ወጥ ማድረግ፣ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች የተሻለ ገቢ እንዲሰበስብ ማድረግና ለቤት ልማቱ አስተማማኝ የበጀት ምንጭ እንዲሆን በማስቻል መንግስት የቤት እጥረትን ለመቅረፍ እያደረገ ላለው ሰፊ እንቅስቃሴ ኮርፖሬሽኑም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡

በመሆኑም ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችል ጥናት በማድረግ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ይፋ ተደርጎ ወደ ተግባር በመግባት በአሁኑ ወቅት ከ 97.5 በመቶ በላይ ደንበኞች ውል ፈጽመውና ከየካቲት ወር ጀምሮ ኪራያቸውን እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ስራው ህጋዊ መሰረት መነሻ ያለውና በመረጃ ላይ ተመስርቶ በጥናትና በጥንቃቄ የተሰራ ቢሆንም በደንበኞች የቀረቡትን ቅሬታዎች በመመርመርና ለሁለት ጊዜ ከፍተኛ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን በዚሁ አግባብ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የ43 ዓመት ታሪክ ለአንድም ጊዜ የኪራይ ተመን ማሻሻያ ሳይደረግ በተለያየ ወቅት እየተጀመረ ሳይሳካ የቆየውን የንግድ ቤቶች የኪራይ ተመን በሙሉ ኃይልና ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁንና የኪራይ ተመን ማሻሻያው ተግባራዊ እንዳይሆን የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል፡፡ የተሻሻለው የኪራይ ተመን ማሻሻያ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ፈታኝ የነበሩ ችግሮችን በትእግስት፣ በጥበብና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፡፡ በዚህ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው ሥራ ህብረተሰቡን ጨምሮ በየሂደቱ ከጎናችን በመሆን ከፍተኛ ድጋፍ የሰጡንን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የኮርፖሬሽናችን የሥራ አመራር ቦርድ፣ የኮርፖሬሽናችን የሥራ ኃላፊዎችና መላው ሠራተኛ እንዲሁም በየወቅቱ መረጃዎችን ተከታትሎ ለህብረተሰቡ በማድረስና ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን የተወጡ መገናኛ ብዙኃን አስተዋጽኦ የተገኘ ውጤት በመሆኑ በኮርፖሬሽኑ ስም ከፍ ያለ መስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

በተያያዘም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ቀደም ሲል የነበረው የሕንጻ እቃዎች አቅራቢ ድርጅት የአደረጃጀት መዋቅር ፈርሶ ከኮርፖሬሽኑ መዋቅር ጋር እንዲቀላቀል ተደርጓል፡፡ የልማት ድርጅቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተዋቅሮ የኮንስትራክሽን ግብአት አቅርቦት ዘርፍ በሚል ስያሜ ኮርፖሬሽኑ ለሚሰራቸው የቤት ልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ግብአቶችን በውስጥ አቅም በማምረትና የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ በማቅረብ ረገድ አስተዋጽኦ ለማበርከት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ኮርፖሬሽናችን የሚገኝበትን የለውጥ እንቅስቃሴ በማገዝ ድጋፍ ላደረጉ በሙሉ የከበረ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዚህ የለውጥ ጉዞ ኮርፖሬሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያረጋገጥኩ በቤት ልማትም ሆነ በቤት አስተዳደር ዘርፍ ተቋሙ እያደረገ በሚገኘው ጥረት የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎችና በተለይም የሚመለከታቸው ተቋማት ከጎናችን በመሆን ያልተቆጠበ ድጋፍና ትብብራችሁን እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!!

አቶ ረሻድ ከማል

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

ዋና ሥራ አስፈፃሚ