መልዕክት መልዕክት

Back

የዋና ሥራ አስፈጻሚ መልዕክት

ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሠለፍ የያዘችውን ራዕይ ለማሣካት ፈርጀ ብዙ ሀገራዊ ልማቶች በረጅምና በአጭር ጊዜ ዕቅድ ነድፋ በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ መላው የሀገራችን ህዝቦችም የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ አቅጣጫ በመረዳት እና በባለቤትነት ስሜት የላቀ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ተጨባጭ ማህበረሰባዊ ለውጦች እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ሀገራችን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ደረጃ ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገሮች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ይህንን ተከትሎ ዜጎቿ መታየት ከጀመረው የእድገት ትሩፋት በየደረጃው ተቋዳሽ መሆን ጀምረዋል፡፡

በከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደተቀመጠው በከተሞች አካባቢ ከሚታዩት ዋና ዋና ችግሮች ውስጥ አንዱ በቂና ምቹ የመኖሪያ ቤት ያለመኖር ነው፡፡ ይህን ችግር መሰረታዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት መንግሰት ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የቤቶች ግንባታ ዘርፍ ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ መስተጋብር በማቀናጀት አያሌ የሥራ እድሎች በመፍጠር ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ባለመ በ10/90 የቤቶች ልማት ፕሮግራም በጣም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ፣ በ20 /80 የቤቶች ልማት ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው፣ በ40 /60 የቤቶች ልማት ፕሮግራም መካከለኛ ገቢ ላላቸው ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም በግሉ ዘርፍ የሚገነቡ /ሪልስቴት/ ቤቶች ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እያቀረበ ህዝቡን የቤት ባለቤት ለማድረግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳትፎ እየሰራ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ለቤት ልማት የሚውል መሬት እያዘጋጀ ቤት የመገንባት አቅም ላላቸው ዜጎች በሊዝ ተወዳድረው ቦታ በማግኘት የራሳቸውን ቤት እንዲገነቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም አሁንም የቤት ፍላጎትና አቅርቦት መሀከል ያለውን ልዩነት ሰፊ በመሆኑ ሌሎች አማራጮች መፈለግ ግድ ሆኗል፡፡ የፌዴራል መንግስት ንብረት የሆኑ ቤቶችን ለረጅም ዓመታት የተለያዩ ስያሜዎች እየተሰጠው ሲያስተዳድር የቆየውን ድርጅት በፊት የነበረው ተግባራትና ኃላፊነቶች ማለትም ቤቶችን የማስተዳደር፣ የመጠገን፣ ማደስና ገቢ የመሠብሰብ ሥራዎች በቂ ያለመሆናቸው ታምኖበት እንደአዲስ በልማት ድርጅት ቅርፅ በማዋቀር ቤቶችን የመገንባትና የማስገንባት ኃላፊነት ተሰጥቶት በዘርፉ ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚል ስያሜ ተቋቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት ኮርፖሬሽኑ የከተማውን ማስተር ፕላን ተከትሎ ቤቶች እየገነባና እያስገነባ በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ የኪራይ ዋጋ የመኖሪያና የንግድ ቤት እንዲያገኙ በማድረግ በግንባታው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በመዲናችን አዲስ አበባ ላይ መሰረታዊ የገፅታ ግንባታ ለማምጣት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከትልቅ ኃላፊነትና አደራ ጋር የተሰጠውን የቤት ልማት ፕሮግራም በብቃት ለመወጣት እና ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ባለድርሻ አካላት በማወያየት ወደ ቅድመ ትግበራ ምዕራፍ ገብቷል፡፡ የቤት ግንባታ ለመጀመርም ኮርፖሬሽኑ ለዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን ማለትም ብቁ የሰው ሀይል ማደራጀት፣ የዲዛይን ዝግጅት ማከናወን፣ የግንባታ መሬት የመለየትና የማዘጋጀት፣ የአፈር ምርመራና ተያያዥ ክንውኖች በቅድመ ትግበራ ምዕራፍ ላይ የላቀ ትኩረት ሰጥቶ እያጠናቀቃቸው የሚገኙ ቁልፍ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ በራሴና በኮርፖሬሽኑ ስም አፅንዖት ሰጥቼ ማስተላለፍ የምሻው መልዕክት ቢኖር ሁላችንም የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች የሀገራችንን ህዳሴ በፅኑ መሰረት ለማኖር በሚደረገው ንቅናቄ ውስጥ የበኩላችን ታሪካዊ አሻራ እንዲኖረን የዘርፉን የአሰራር ሥርዓት በማሻሻል፣ አዳዲስ ቤቶችን በመገንባት ተደራሽ በማድረግ የተገልጋይ እርካታ ለማሳደግ “የህዳሴውን ቤት እንገነባለን” በሚል መሪ ቃል ከመቼውም ጊዜ በላቀ ተነሳሽነት ተቋማዊ ችግሮችን ፈተን አጠናቅቀን ትርፋማ የልማት ድርጅት እንደምንሆን ያለኝን ፅኑ እምነት መግለፅ እወዳለሁ፡፡

በመጨረሻም ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዘርፉ ውጤታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኮርፖሬሽኑ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ይደግፉ ዘንድ መልዕክቴን ከአክብሮት ጋር አስተላልፋለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!!

አቶ ረሻድ ከማል

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

ዋና ሥራ አስፈፃሚ