ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሪፎርም ስኬት ጎበኙ

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበላይ ጠባቂው ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ እየተመራ በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ኮርፖሬሽኑ ባስመዘገባቸው የሪፎርም ስኬቶች ዙሪያ የግማሽ ቀን ጉብኝት አካሄደ፡፡
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ለጉባኤው አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ኮርፖሬሽኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገባቸው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስኬቶችና ምክንያቶቻቸው ለጉባኤው አባላት ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአገርዓቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት የራሱን ራዕይ አስቀምጦ ለከፍተኛ ለውጥ እየተጋ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ኮርፖሬሽኑ እያካሄደ ያለውን የሪፎርም ሥራ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በበኩላቸው የኮርፖሬሽኑ የለውጥ ሂደት አርአያነት ያለው ተግባር በመሆኑ ለተጨማሪ ስኬት እንዲተጋ አስገንዝበዋል፡፡
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ የቤት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ ችግር ለመቅረፍ፤ በቤት ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በመገንባት ላይ መሆኑን የተገነዘቡት የጉባኤው አባላት ኮርፖሬሽኑ የያዛቸውን ስኬቶች ጠብቆ ለላቀ ውጤታማነት አበክሮ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡