ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

ኮርሬሽኑ ለሁሉም ደንበኞቹ በሚያዚያ ወር የኪራይ ክፍያ የአምሳ በመቶ ቅናሽ አደረገ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በኪራይ በሚያስተዳድራቸው 18, 153 የመኖሪያ፣ የንግድና የድርጅት ቤቶች የኮቪድ 19 ኮረና ቫይረስ በፈጠረው ተፅእኖ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ለተጎዱ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ለሚገኙ ደንበኞቹ የሚያዚያ ወር የኪራይ ወርሃዊ ክፍያ የአምሳ በመቶ ማለትም የእያንዳንዱ ተከራይ የወርሃዊ ክፍያዉን ግማሽ ተቀናሽ አደረገ፡፡ ይህ ተቀናሽ የሚያዚያን ወር ብቻ የሚመለከት ሲሆን ኮርፖሬሽኑ የቫይረሱን ስርጭት በደንበኞቹ ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ በየወሩ እየገመገመ የሚቀጥሉትን ወርሃዊ ክፍያዎች መጠን ለደንበኞቹ በሚዲያ እንደሚያሳውቅ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማል ሚያዚያ 2/ 2012 ከጥዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ለግሃር በሚገኘው በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት በቢሮዋቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ገልጸዋል፡፡ ይህ ለኮርፖሬሽኑ የማይከፈል አጠቃላይ ቅናሽ በኮርፖሬሽኑ የሚፈጥረዉን ተጽእኖ በብር ሲሰላ በሚያዚያ ወር ሊሰበሰብ ከታቀደው 120 ሚሊዮን ብር ግማሹ ማለትም 60 ሚሊዮን ብር ገቢ ተቋሙን ያሳጣዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው መጋቢት 22 ኮርፖሬሽኑ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለኮቪድ 19 ብሄራዊ የድጋፍ አሰባሰብ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ክቡር ሥራ አስፈጻሚው በመግለጫቸው እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ ባደረገው የሚያዚያ ወር የኪራይ ቅናሽ ከኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤት ተከራዮች የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ባሻገር በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ሆቴሎች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሸቀጣሸቀጦች፣ መጋዘኖች፣ ዎርክሾፖች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ቢሮዎች እና ሌሎች የተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ የቫይረሱ ስርጭት ተፅእኖ የፈጠረባቸው የኮርፖሬሽኑ ደንበኞች የተደረገው ቅናሽ የተወሰነ እፎይታ ይሰጣል፡፡ ይህ ፈታኝ ወቅት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምናልፈው ያላቸውን እምነት አክለው ገልጸዋል፡፡
 ሙሉ ዜናውን እዚህ ያገኛሉ (ኢ.ቲ.ቪ)