ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

ኮርፖሬሽኑ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለመዘርጋት ዝግጅት እያደረገ ነው

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተቀናጀ የመረጃ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችለውን ዝግጅት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ወርቁ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የዘልማድ አሰራር በመቀየር አሰራሩን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማገዝ ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችለውን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አሰራሩ የመረጃ አያያዝን፣ አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመን ተወዳዳሪ ተቋም ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው የተቀናጀ የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሥርዓት ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ በሂደት ላይ የሚገኘው የተቀናጀ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሥርዓት በስድስቱም የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት በሥራ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከማዕከላዊ ሰርቨር ጋር የተገናኘ ሰርቨር እንደሚተከል ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱም ከየካቲት ወር ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡