ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

Back

ቋሚ ኮሚቴው የኮርፖሬሽኑን መስሪያቤቶችና የቤት ግንባታ ሳይት ጎበኘ

ቋሚ ኮሚቴው የኮርፖሬሽኑን መስሪያቤቶችና የቤት ግንባታ ሳይት ጎበኘ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መስሪያ ቤቶችንና የግንባታ ሳይትን ጎበኘ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤትና በስሩ ከሚገኙ ስድስት ቅርንጫፎች መካከል ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ቅርንጫፍ 4 ጽሕፈት ቤት በመገኘት ጉብኝት ካካሄደ በኋላ ከአመራሮችና ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው ከኮርፖሬሽኑ በርካታ ሳይቶች መካከል አንዱ በሆነው በጦር ኃይሎች አካባቢ በተለምዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክበብ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ የተጀመረውን የቤት ግንባታ ጎብኝቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል የኮርፖሬሽኑ የዜጎች ቻርተር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታት፣ የአመራሮች እና የሠራተኞች ግንኙነት፣ የሪፎርም ሥራዎች፣ የንብረትና በጀት አጠቃቀም፣ የመረጃ አያያዝ፣ የቤት ልማት እንቅስቃሴዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ኮርፖሬሽኑ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ተጠናክረው መቀጠል የሚገባቸውን እና መሻሻል ይኖርባቸዋል ያሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞችም በበኩላቸው በተለይም በቤት ልማት ዙሪያ ከግንባታ ቦታዎች እና ቤት ማስመለስ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ውስብስብና በኮርፖሬሽኑ የተናጠል እንቅስቃሴ ብቻ የማይቀረፉ በመሆናቸው የቋሚ ኮሚቴው ብርቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡