ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

Back

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ/የድርጅት ቤቶች የኪራይ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ በደንበኞች ለቀረቡ ቅሬታዎች የተሰጠ ምላሽና ውሳኔ::

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ/የድርጅት ቤቶች የኪራይ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ በደንበኞች ለቀረቡ ቅሬታዎች የተሰጠ ምላሽና ውሳኔ

ሀ. የኪራይ ማስተካከያው ያስፈለገበት ምክንያትና የተደረጉ ጥናቶች ውጤት፣

 
 1. ኮርፖሬሽኑ የኪራይ ትመና ለማድረግ መነሻ ያደረገው ለረዥም ዓመታት አንዳችም የኪራይ ጭማሪ ሳያደርግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ለገበያ ምቹ በሆኑ ቦታዎች ማለትም መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ስቴድየም፣ ብሔራዊ፣ ቦሌ፣ አራት ኪሎ ወዘተ... በመሳሰሉት የከተማው እምብርት ላይ የሚገኙ ታዋቂ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎች፣ ኬክ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬቶች በአማካኝ ከብር 200 እስከ 3000 በወር ክፍያ በኮርፖሬሽኑ ቤት ሲሰሩ ከግለሰብ ተከራይተው በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች በአማካኝ ከብር 20,000 እስከ 150,000 ከፍለው በተመሳሳይ ዋጋ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን ዋና ዋና ምክንያቶች መሰረት በማድረግ የኪራይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
 2. ኮርፖሬሽኑ የተጣለበትን ተግባርና ሀላፊነት መወጣት የሚጠበቅበት በመሆኑ፣
 3. ጤናማ የገበያ ውድድርን ለማጎልበት፣
 4. ሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ለማረጋገጥ፣
 5. የኪራይ ተመን አሰራሩን ለማስተካከልና ወጥ ለማድረግ፣
 6. ከኪራይ ከሚሰበሰበው ገቢ ተጨማሪ ቤቶችን በመገንባት እድሉን ላላገኙ ዜጎች እድል ለመፍጠር ሲሆን ከዚህ በመነሳት በኮርፖሬሽኑ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ሳይንሳዊ በሆነ እና በርካታ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በቂ መረጃ በማሰባሰብና በመተንተን የኮርፖሬሽኑ፣ የመንግስትና የግሉ ማህበረሰብ የንግድ ቤት የኪራይ ተመን መጠን በማነፃጸር እንዲሰራ ተደርጓል፡፡
 7. የጥናቱ ውጤት ያመላከተው የግሉ ዘርፍ የሚያስከፍለዉ በ1 ካሬ/ሜ ከ420 ብር እስከ 2900 ብር ሲሆን አማካዩ ብር 848 መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአንጻሩ የኮርፖሬሽኑ የ1 ካሬ ሜትር ዋጋ ሲታይ በካ/ሜ ከ 0.1 እስከ ብር 71 መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
 8. ከዚህ በመነሳት ከላይ የተጠቀሱ ነባራዊ ሁኔታዎች ባገናዘበ መልኩ የንግድ/ቤቶች የኪራይ ተመን የግሉ ማህበረሰብ የንግድ ቤቶች ኪራይ ተመን አማካይ ዋጋ በመውሰድ ከግሉ ተመን 40% እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡
 9. ከዚህ በተጨማሪም 3 ቅንስንናሾች ማለትም፡-
  I. እንደ ቤቶቹ የጥራት ደረጃ (እስከ 30%)፣
  II. ለንግድ ስራ ያላቸው አመቺነት (እስከ 30%) እና
  III. እንደቤቶቹ ስፋት (እስከ 75%) ከግንዛቤ ያስገባ ቅንስናሾች ተደርገዋል፡፡
  በአጠቃላይ የተወሰደው የካሬ ሜትር የኪራይ ተመን ከግሉ ከ50% በታች መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ለ. ለቅሬታዎች የተሰጠ ምላሽና ውሳኔ

የተተመነው ኪራይ ፍትሀዊ ቢሆንም የደንበኞችን ቅሬታ ማድመጥ ተገቢ በመሆኑ በኮርፖሬሽኑ እና በስራ አመራር ቦርድ በኩል ታይቶ ለቀረበው ቅሬታ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
 1. በእያንዳንዱ የንግድ ቤት የተተመነውን አዲሱን የኪራይ ተመን በ3 ዓመት ከፋፍሎ አዲሱን የኪራይ ተመን በ3ኛው ዓመት ላይ እንዲደርሱበት ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረት
  I. 1ኛው ዓመት ላይ አሁን እየከፈሉ የሚገኙትን እና የተተመነውን ተጨማሪ ኪራይ 35% እንዲከፍሉ፣
  II. 2ኛ ዓመት ላይ አሁን እየከፈሉ የሚገኙትን እና የተተመነውን ተጨማሪ ኪራይ 70% እንዲከፍሉ፣
  III. 3ኛ ዓመት ላይ አሁን እየከፈሉ የሚገኙትን እና የተተመነውን ተጨማሪ ኪራይ 100% እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
 2. የንግድ ያልሆኑ የድርጅት ቤቶች በተለይም ለቢሮ አገልግሎት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ አካል ጉዳተኞች፣ ለሀይማኖት ተቋማት፣ ለፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለሙያ ማህበራት፣ ለሴቶችና ወጣቶች ሊግ፣ ለትርፍ ላልተቋቋሙ ድርጅቶች፣ ተቀምጦ የነበረው በካ/ሜ ብር 339 በካ/ሜ ወደ ብር 140 ብር ዝቅ እንዲል ተወስኗል፡፡
 3. አንዳንድ በልዩ ሁኔታ መታየት የሚገባቸው ካሉ እየተጠና በኪራይ ትመና መመሪያ መሰረት በልዩ ሁኔታ በኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር ደረጃ ታይቶ እልባት እንዲሰጠው ተወስኗል፡፡
 4. የንግድ ቤት ቁልፍ ገዝተው የስም ዝውውር ሳያደርጉ አሁንም በቀደመው ተከራይ ስም ውል እየፈጸሙ የሚገኙ ግለሰቦች በአዲሱ የኪራይ ተመን መሰረት ከላይ በቁጥር አንድ በተቀመጠው የኪራይ ተመንና የአከፋፈል ስርዓት መሰረት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡
 5. በተራ ቁጥር 4 የተወሰነው እንደተጠበቀ ሆኖ ሽያጩ በውልና ማስረጃ ከተወሰነበት ጊዜ አንስቶ ያለውን የውዝፍ አከፋፈሉ በቀጣይ እንዲገለጽ ተወስኗል፡፡
 6. የውል እድሳት ይከፈል የነበረው ብር 500 ለአንድ ጊዜ ቀሪ ሆኖ ያለክፍያ ውል እንዲታደስ ተወስኗል፣
 7. ከንግድ ቤት የዘርፍ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ዘርፍ ለመለወጥ ለሚፈልጉ ደንበኞች ለአንድ ጊዜ ለዘርፍ ለውጥ ይከፈል የነበረው ብር 7000 እንዲቀር ተደርጓል፡፡
 8. አዲስ ውል ሲፈጸም ለዋስትና ይያዝ የነበረው የ3 ወር የኪራይ ዋጋ ዲፖዚት ለአንድ ጊዜ እንዲቀርና በነበረው የማስያዣ ገንዘብ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
 9. በውጭ ምንዛሪ የሚከራዩ ቤቶች ላይ የተደረገው 92 ዶላር የካ/ሜትር ተመን ወደ 50 ዶላር እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡
 10. አዲሱ የኪራይ ተመን ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነው ውሳኔ ቀርቶ ተጨማሪ የአንድ ወር የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቶ ከየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን
ታህሳስ 25 ቀን 2011