ዜና ፌ.ቤ.ኮ ዜና ፌ.ቤ.ኮ

በቤት አስተዳደር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለመንግስት ተሿሚዎችና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የመኖሪያና የድርጅት ቤቶችን በማቅረብ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም ባሻገር፣ የቤቶቹን ወርሃዊ የኪራይ ገቢ በመሰብሰብ ለመንግስት የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ጉልህ ሚና አበርክቷል፡፡ ለኮርፖሬሽኑ የሚቀርቡ የቤት ጥያቄዎችን መረጃ አደራጅቶ በመያዝ፣ በተለያዩ መልክ የሚገኙ ቤቶችን ለመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ቅድሚያ በመስጠት የመደልደል፣ ቤቶችን በጨረታ መነሻ ወይም በጨረታ የማከራየት፣ የቤቶቹን የውል ዕድሳት ማከናወን፣ በተለያዩ ጊዜያት ለሚቀርቡ የሥም ዝውውርና የዘርፍ ለውጥ ህጋዊነት በማረጋገጥ ውል እንዲፈፅሙ በማድረግ በዕቅዱ ውስጥ አካቶ ውጤታማ አገልግሎት ለደንበኞቹ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የቀረበለትን የ8ዐ3 የቤት ጠያቂዎች መረጃ አደራጅቶ ይዟል፡፡ በተለያየ መልክ የሚገኙ 15ዐ ቤቶች እንዲከራዩ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የ146 ባዶ ቤቶች ሪፖርት ቀርቦ ከነዚህ ውስጥ ለመንግስት የሥራ ሃላፊዎች 135 ቤቶች ተደልድለው ውል እንዲሞላባቸው ተደርጓል፡፡ የድርጅት ቤቶች በጨረታ መነሻ ወይም በጨረታ እንዲከራዩ ለማድረግ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት በመንግስት በተሰጠ ውሳኔ 18 የድርጅት ቤቶች በጨረታ መነሻ ዋጋ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተመደበ ሲሆን የሌሎች ባዶ ቤቶች መረጃቸው ተሟልተው መያዛቸው ታውቋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች ውስጥ በ927ዐ ቤቶች ላይ ወቅታዊ የመስክ ክትትል በማድረግ ህገወጥነትን ለመከላከል እንዲቻል በተያዘው ዕቅድ መሠረት በ7465 ቤቶች ላይ የመስክ ክትትል ተደርጓል፡፡ በክትትሉም በተገኘው ውጤት መሠረት አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የደንበኞችን ህጋዊነት በመስክና ከማህደር በማረጋገጥ የመኖሪያና የድርጅት ቤቶችን በድምሩ 6152 ቤቶች ላይ ውል ዕድሳት ተከናውኗል፡፡ የኮርፖሬሽኑን ቤቶች ቆጠራ ለማከናወንና መረጃዎችን ወቅታዊ የማድረግ፣ ለሚቀርቡ ቤት ነክ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት፣ ካርታ ላልወጣላቸው ቤቶች ካርታ የማውጣትና የማስተካከል፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ማረጋገጫ ሰርተ ፊኬት የማውጣት፣ ለቤቶች የዋጋ ተመን ማዘጋጀት፣ በተለያዩ ምክንያት በልማት ለፈረሱ ቤቶች ካሳ በማስከፈልና እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ከኮርፖሬሽኑ አስተዳደር የሚወጡ ቤቶችን መረጃ በማደራጀት ሙሉ በሙሉ ከንብረት እንዲሰረዙ በማድረግ የቤቶችን መረጃ የተሟላ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም፡- የኮርፖሬሽኑን ቤቶች ቆጠራ በማድረግ ትክክለኛውን የቤቶች መረጃ ለመያዝ ከተለያዩ አካላት ልምድ ተወስዶ ዕቅድና የቅፅ ዝግጅት ተጠናቆ ቆጠራውን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁ ታውቋል፡፡ ካርታ ላልወጣላቸው 2229 ቤቶች መረጃቸውን በማጣራት ካርታ እንዲወጣላቸው ለማድረግ በስድስት ወራት ውስጥ በታቀደው መሠረት የ2293 ቤቶች መረጃ ተጠናክሮ ለከተማው አስተዳደር ተልኳል፡፡ ለኮርፖሬሽኑ ለቀረቡ 4997 ቤት ነክ ጥያቄዎች መረጃዎችን በማጣራትና ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ ወቅታዊ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ መረጃውን በማጣራት ካርታ እንዲወጣላቸው ለአዲስ አበባ መስተዳደር ከተላኩት የቤት ዝርዝሮች ውስጥ የ455 ቤቶች ካርታ ሙሉ በሙሉ አልቆ ርክክብ የተደረገ ሲሆን፣ በድሬዳዋ የ74 ቤቶች ካርታ ተሰርቶ ርክክብ ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ካርታ የወጣላቸውን የ4ዐዐዐ ቤቶች መረጃ የምዝገባ ሰርተፊኬት እንዲሰራላቸው ለማይንቀሳቀስ ንብረት ማረጋገጫ ጽ/ቤት ለማቅረብ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የ4717 ቤቶች ተጠናቅሮ ለጽ/ቤቱ ቀርቧል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የ432 ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተጠናቀው ኮርፖሬሽኑ መረከብ መቻሉ ታውቋል፡፡ በቀሪዎችም ላይ ክትትሉ ቀጥሏል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከኮርፖሬሽኑ አስተዳደር የወጡ ቤቶችን መረጃ በማደራጀት ፈርሰው ካሳ የተከፈለባቸውንና ያልተከፈለባቸውን ቤቶች በመለየት መረጃውን አደራጅቶ ለመያዝ በታቀደው መሠረት የ867 ቤቶች መረጃ ተደራጅቶ ተይዟል፡፡ የካሳ ክፍያቸው ገቢ መደረጉን እየተረጋገጡ ካሉ 32ዐ ቤቶች ውስጥ የካሣ ክፍያቸው በትክክል ገቢ የሆኑ የ8ዐ (4ዐ%)ቤቶች ዝርዝር እንዲሰረዝ ለውሳኔ መቅረቡ ተረጋግጧል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው የመኖሪያ፣የድርጅት ቤቶችና ሽንሽኖችን መረጃ ወቅታዊ የማድረግ ሥራም ተሰርቷል፡፡